የኢስላሚክ ፋይናንስ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሙከራ ትግበራ ዳሰሳ ጥናት ይፋ ሆነ!!

 በወራቤ ዲስትሪክት ጽ/ቤት ሥር ባሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቀደም ብሎ በአንድ መስኮት ብቻ የሙከራ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ  የአሠራር መመሪያ መነሻ ያደረገ የዳሰሳ ጥናት  ቀርቧል።

በዳሰሳ ጥናት መድረኩ ላይ የዑለማ አማካሪ የኃማኖት አባቶች፣ የዋና መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞን፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ስትሪንግ ኮሚቴ አመራር አካላት፣ ባለሙያዎች፣ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ውይይት አድርገዋል።

የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት በዋና መስሪያ ቤት የብድር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተገኝወርቅ ሰራዊት የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ማከናወን ከሚጠበቅባቸው ተግባራት አንዱ የፋይናንስ አካታችነት እንደመሆኑ መጠን የወለድ አልባ የዱቤ ግብይትና ቁጠባ አገልግሎት አማራጭ ለማቅረብ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሁ መነሻ በዘርፉ የተጀመረውን የሙከራ ትግበራ  በጠንካራና ደካማ ጎን የሚነሱ ተግባራት በአካላዊ ዳሰሳ ተለይቷል ያሉት አቶ ተገኝወርቅ ማስተካከያዎችን በማድረግ አገልግሎቱን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገር ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ዳሰሳ ጥናት ወራቤ፣ ላንፉሮ፣ ምዕራብና ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ቅ/ጽ/ቤቶች በአካላዊ ዳሰሳው የተሸፈኑ ናቸው።

የወራቤ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ነጃ ሙዴ እንዳሉት በገጠር ለአርሶአደሩ በከተማ ደግሞ ለስራ አጥ ወጣቶች፣ ሴቶች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የብድር አቅርቦት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህል በማጎልበት የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ መለወጥ የኦሞ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማዊ ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ77 ሚሊየን ብር በላይ ወለድ አልባ የፋይናንስ አቅርቦት እና የተጣራ ቁጠባ ከ54 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል። ከ21ሺህ በላይ የወለድ አልባ የቁጠባ ደንበኛ ማፍራት የተቻለ ሲሆን የወለድ አልባ ፋይናንስ አገልግሎት ጠቅለላ ሽፋን በ2011 በጀት ዓመት 7% ከነበረበት ወደ 65% በማሳደግ ጅምር ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉንም አስረድተዋል።

የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ኃ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው የተቋሙን የወለድ አልባ የፋይናንስ አቅርቦት አሰራሮችንና መመሪያዎችን በማስጠበቅ የፋይናንስ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ስርአት ተግባራዊ በማድረግ የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የተገልጋይ እርካታን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስታያየት በተቋሙ የተደረገው ጥናት ጅማሮ የሚበረታታ መሆኑን በመግለፅ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ይበልጥ ለማጥራት ጥናቱ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።