ወጣቶችን የስራ ዕድል ፈጠራ ከፋይናንስ ተጠቃሚነት ጋር አቀናጅቶ በመምራት ኢኮኖሚያቸውን በማሳደጉ ተግባር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

ቀን 26/06/2016ዓ.ም
ኦሞ ባንክ ቀደም ሲል ከተለያዩ ክልሎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ጋር በጋራ ለማከናወን ስምምነት ላይ መድረሱን ተከትሎ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መዋቅር ጋር በአርባምንጭ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት የዘገዩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ግቦችን ለማሳካት ከኦሞ ባንክ ጋር በቅንጅት መስራት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ተናግረዋል።

ለወጣቶች ከመነሻ ፋይናንስ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከኦሞ ባንክ ጋር በተገባው የጋራ ግብ ስምምነት መነሻ ወደ ውጤት ለመቀየርና ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከባንኩ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ በተደረሰባቸው አንኳር የሥራ ዕድል ፈጠራና የባንኩ ቅንጅታዊ ስራዎች በሁሉም የዞንና ወረዳ መዋቅሮች ወርዶ በልዩ ክትትል የመረጃ ልውውጥ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ባንኩ ለሁሉም ህብረተሰብ የፋይናንስ መደላድል በመፍጠር ከኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲላቀቁ ከመስራት ሌላ ተልዕኮ እንደሌለው የተናገሩት ደግሞ የኦሞ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም አላሮ ናቸው።

በቁጠባ ሀብት በማሰባሰብ የብድር ተጠቃሚ ማድረግ የባንኩ ዋንኛው ተግባር መሆኑን ያብራሩት ፕሬዝዳንቱ ባንኩ የህዝብ ገንዘብ አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን በተበዳሪዎች እጅ የሚገኝ ገንዘብ ያለመመለስ ዕድል አይኖረውም ብለዋል።

ይህንኑ ተመላሽ የገንዘብ ሀብት በማሰባሰብና የወጣቶችን ትክክለኛ ፍላጎት ለይቶ ወደ ስራ ለማስገባት በባንኩና በስራ ዕድል ፈጠራ መዋቅር እንዲሁም ከሌሎች መዋቅሮች ጋር ብርቱ ቅንጅታዊ ስራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ይህ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ የዞን አስተዳደርና የፍትህ መዋቅሮች ጋር የተካሄደው የጋራ መድረክ ቀደም ሲል ባንኩ በጋራ ለማካሄድ ባስቀመጠው መርሀ-ግብር መሠረት የተካሄደ ሲሆን የየዞኑ አስተዳደር፣ የክልሉን ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ፍትህ መምሪያዎችንና ፖሊስ ኮሚሽንን ያካተተ መድረክ ነው።

ኦሞ ባንክ የሁላችንም ባንክ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *