ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በ2013 ስድስት ወራት 57 ሚሊዮን የተጣራ ብር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት በሻሽመኔ ከተማ አካሄደ፡፡

ተቋሙ በስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙ ከሌሎች ወቅቶች የተሻለ ስለመሆኑ በግምገማው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለ ድርሻ አካላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሻሽመኔ ከተማ ላይ የተካሄደው የስድስት ወራት ዕቅድ ግምገማ የተጀመረው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዓለማየሁ ኃ/ጊዮርጊስ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነበር፡፡ አቶ ዓለማየሁ በመክፈቻ ንግግሩ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ የዜጎችን ማህበራዊ ህይወት ለማሻሻልና በሀገር አቀፍ እንዲሁም በክልል ደረጃ የተረጋጋ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ማምጣት በሚያስችል ሁኔታ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ በመቀጠልም በተቋሙ መሠረታዊ ለውጦችን ማምጣት የሚያስችሉና ውስጣዊ የአፈጻጸም አቅሞችን መገንባት የሚያስችሉ አስራ ስምንት መመሪያዎችንና ደንቦችን እስከ ታችኛው አደረጃጀት በማውረድ አዎንታዊ ለውጦችን እውን ለማድረግ በትጋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው አያይዘው በተቋሙ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጥናትና በምርምር ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ተቋሙ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አመልክተው በተለይም በብድር አመላለስ ዙሪያ እያጋጠሙ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል በየአደረጃጀቶቹ አመራሩ በራሱና በቤተሰቡ ተበዳሪ ሆኖ መገኘቱ በአንዳንድ አከባቢዎች ችግሩን እያወሳሰበ እንደሆነ ለዚህም  የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ድጋፍ በእጅጉ ተፈላጊ መሆኑን ትኩረት በመስጠት ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ የቀረበው የዓመቱ ስድስት ወራት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ተቋሙ በአብዘኛዎቹ የእቅድ አፈጻጸሞች ተስፋ ሰጪ እመርታዎችን አስመዝግቧል፡፡ የተቋሙ ዋና ዋና ተግባራት በሆኑት ደንበኛ ማፍራት፣ በማስቆጠብና በብድር ስርጭት እንዲሁም በብድር ማስመለስ ተቋሙ ተጨባጭ መሻሻሎችን ማሳየቱ ተብራርቷል፡፡

በዚህም መሠረት ሪፖርቱ እንዳመለከተው በበጀት ዓመቱ በተቋማዊ የቁጠባ አፈጻጸም 312 ሚሊዮን ብር የተጣራ ቁጠባ ለመሰብሰብ ታቅዶ 141.1 ሚሊዮን (45%) መሰብሰብ መቻሉ የተገለጸ ሲሆን አዲስ የቁጠባ ደንበኛ በማፍራት ረገድም 338,518 ደንበኛ ለማፍራት ታቅዶ 167,298 (49%) ተግባራዊ መደረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡ በሪፖርቱ ላይ የወንዶችና ሴቶች ደንበኛ ቁጥር ተለይቶ የተገለጸ ሲሆን በዚህም መሠረት በስድስት ወራት አፈጻጸም የወንዶቹ 42 የሴቶቹ ደግሞ 35 ከመቶ ድርሻ እንዳለው ተመልክቷል፡፡

ተቋሙ ለሁለት ማለትም ለደቡብና ሲዳማ ክልሎች የቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን የሚሰጥ በመሆኑ የሁለቱም ክልሎች የቁጠባ አፈጻጸም በየመዋቅሩ ሲታይ የደቡብ ክልሉ የዕቅዱን 141 እንዲሁም የሲዳማው ደግሞ 52 ከመቶ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተብራርቷል፡፡

በብድር ደንበኛ ረገድም ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 72,398 ደንበኞችን ለማፍራት አቅዶ 34060 (47%) ከመቶ አፈጻጸም መመዝገቡን፣ 1.022 ቢሊየን ብር ብድር ለማሰራጨት ዕቅድ ተይዞ 953.2 ቢለዮን (93%) ተግባራዊ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ብድር አመላለስን አስመልክቶ 918.8 ሚሊዮን ብር ለመመለስ ታቅዶ 833.9 (91%) አፈጻጸም መመዝገቡም እንዲሁ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመድረኩ ላይ የውዝፍ ብድር አስመላሽ ግብረ ኃይል መመሪያ ማስፈጻሚያ ቀርቦ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተሳታፊዎቹ መመሪያ የበለጠ ውጤታማ የሚሆንባቸውንና ሊዳብሩ ይገባሉ ያሏቸውን አስተያየቶች በግብዓትነት አቅርበው ተቋሙም የቀረቡ አስተያየቶችን ተቀብሎ ማሻሻያዎችን እንደሚያደረግ የሚገልጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

 በዚሁ በሻሽመኔ ከተማ በተካሄደው የተቋሙ የስድስት ወራት የአፈጻጸም መድረክ ላይ ከደቡብና ሲዳማ ክልሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻና አጋር ከፍተኛ አካላትና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ በደቡብና በተለይም ደግሞ በሲዳማ ክልል ወደኋላ የቀሩ አከባቢዎችን የመደገፉንና የመከታተሉን ስራ አጠናክሮ መሄድ እንዳለበት እንዲሁም ተቋሙ በገጽታ ግንባታ ረገድ  በመልካም ጅምር ላይ ያሉ አፈጻጸሞችን እያሰፋ መሄድ እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የመረጃ ስርዓቱን ለማዘመን የተደረገው ጥረትም አበረታች መሆኑ የተገመገመ ሲሆን በቁጠባም ሆነ በብድር አገልግሎቶች የሴቶችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ አሠራሮች መዘርጋት እንዳለባቸውም የስብሰባው ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ በመጨረሻም በመድረኩ ላይ ከነበሩ ባለድርሻ አካላቱ ተሳትፎ የቀረቡ ገንቢ አስተያየቶች ለቀሪዎቹ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እጅግ ጠቃሚ ግብዓቶች   መሆናቸውን በመግለጽ የዕለቱ ስብሰባ አብቅቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *