ባለፉት ስድስት ወራት ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀትና የፎርክሎዠር መመሪያን በመተግበር 93.9 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ማስመለስ መቻሉ ተገለፀ ::

በ 2013 ግማሽ ዓመት በክስ ፣ በመደበኛ ማስጠንቀቂያ ፣ በፎርክሎዠር እና ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ከውዝፍ ብድሮች 93.9 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አስታወቀ ::

የተቋሙ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየለ አዘራ እንደገለፁት ÷ ተበዳሪዎች በገቡት ዉል መሠረት ብድሩን መክፈል እየቻሉ ያልከፈሉ ተበዳሪዎችን ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በህግ ከሶ ማስመለስ አንዱ የህግ ማስከበር ሥራ አካል ነው፡፡

በፍ/ቤት ክስ አቀርቦ ውዝፍ ከማስመለስ ባሻገር ቅ/ጽ/ቤቶች ከየመዋቅሩ የፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ብድር እንዲያስመልሱ ከመዋቅሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቀላጠፍ እና ድጋፍ በማድረግ ውዝፍ እንዲመለስ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ ÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የፎርክሎዠር መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል ::

በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በተቋሙ የህግ ባለሙያዎች በክትትል ላይ የሚገኙት በማህበራት እና በግለሰብ ደረጃ  አዲስ ክስ የተመሰረተባቸው እና  ከ2012 በጀት ዓመት የተዘዋወሩ 44.4ሚሊዮን ብር የገንዘብ መጠን ከያዙ 451 መዝገቦች  በፍርድ ቤት አፈጻጸም ፋይል 9.3 ሚሊዮን ብር ÷ በመደበኛ ማስጠንቀቂያ 26.9 ሚልዮን እንዲሁም የፍርክሎዠር መመሪያን በመተግበር 35.4 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ::

በየደረጃዉ ከሚገኘዉ    የፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት በግማሽ ዓመቱ 22.1ሚሊዮን  ብር ማስመለስ እንደተቻለም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል :፡

የተሰጣቸዉን የሥራ ኃላፊነት ተጠቅመዉ የተቋሙን ሀብት እና ንብረት የመዘበሩ ሠራተኞች እርምጃ እንዲወሰድባቸዉ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ÷ የተመዘበረው የሕዝብና የመንግስት ሀብት እንዲመለስ እየተሰራ  እንደሚገኝም ተናግረዋል ::

በዚህ መሠረት በአጠቃላይ  በግማሽ በጀት ዓመት 13.2 ሚሊዮን ብር የያዙ 97 መዝገቦች በክትትል ላይ ሲገኙ ÷ በፍርድ ቤት በነባር አፈፃፅም ፋይል 1.4 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ÷ በኦዲት ከተረጋገጡ ጉዳዮች እና ተሰብሳቢዎች ከክስ በፊት በድርድር  1.9 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል ::

ተቋሙ በሚከሰስባቸዉ በተለይም በሥራ ክርክር ጉዳዮች ተቋሙን በመወከል ምላሽ በመስጠት ያላግባብ ክፍያዎች እንዳይፈጸሙ እና ህገ ወጦች ወደ ተቋሙ ዳግም እንዳይመለሱ እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ፡፡

በግማሽ በጀት ዓመቱ ባጠቃላይ 19 ሰራተኞች እና የስራ መሪዎች  የስራ ውላችን ከህግ ውጪ ተቋርጧል በማለት ተቋሙን የከሰሱ ሲሆን  ከመዝገቦቹ መካከል  6 ለተቋሙ የተወሰነ፤ 2 መዝገቦች ለከሳሾች የተወሰነ እንዲሁም 11 መዝገቦች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች አሁንም በሂደት ላይ ይገኛሉ ፡፡

በተጨማሪም በልዩ ልዩ ክሶች በጂንካና በዲላ ዲስትሪክቶች ካሉ አራት መዝገቦች 3.2 ሚሊዮን ብር ለተቋሙ መወሰኑን  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ::

በግማሽ በጀት ዓመቱ የተሠራዉ ሥራ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ በቀጣይ ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚገባ፤ በተለይም የፎርክሎዠር መመሪያን በሚገባ በመተግበር የተቋሙን ዉጤታማነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *