በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኢኮኖሚው ተጠቃሚ ለማድረግ የጋራ ኃላፊነት መወጣት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡

ኦሞ ባንክ ከአራቱ ክልሎች ማለትም ከሲዳማ፣ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጽያ እና ከማዕከላዊ ኢትዮጽያ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት የሚያስችሉ አገልግሎቶችን ውጤታማ ለማድረግ ከስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ጋር በጋራ ኃላፊነት በሚወሰዱ ጉዳዮች ተግባብቶ መስራት ወሳኝነት እንዳለው የኦሞ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም አላሮ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በጋራ ሥራዎች መረጃ ልውውጥ ወቅት ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮችን መሠረት ያደረጉ ሥልጠናዎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ በዚህ መድረክ ተሳታፊ የነበሩ የኦሞ ባንክ ቦርድ አባልና የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀገረጽዮን አበበ በበኩላቸው ባንኩ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ካለው ፋይዳ ባሻገር ለመላው ህብረተሰብ ሀብት መፍጠሪያ ባንክ አድርጎ ለመጠቀም እንዲቻል በጋራ ጉዳዮች በቅንጅት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም የቢሮ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያየት የጋራ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተፈጠረው የባንኩ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራ ይዝ ቅንጅታዊ አሰራር ወደ ታችኛውም መዋቅር ፈጥኖ መውረድ እንዳለበትና በዚህ መድረክ የጋራ የተደረጉ ስምምነቶችን አክብሮ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአራቱም ክልሎች ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊዎች ከባንኩ ፕሬዝዳንት ጋር በ2016 ዓ.ም ቀሪ 5 ወራት ተግባራዊ በሚደረጉ ሥራዎች ዙሪያ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ የጋራ ስምምነቱ በመርሀ-ግብሩ መሠረት ወደ ታችኛው መዋቅር የሚወርድ ሲሆን በባንኩ ዲስትሪክቶችና የኢንተርፕራይዝ መምሪያ፣ በባንኩ ቅርንጫፍ እና ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤቶች አስፈፃሚነት ተሳታፊ አካላቶችን ጨምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ኦሞ ባንክ የሁላችንም ባንክ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *